የቤተ ክርስቲያን ኅብረት ከትናንት እስከ ዛሬ የመጨረሻ ክፍል

የቤተ ክርስቲያን ኅብረት ከትናንት እስከ ዛሬ የመጨረሻ ክፍል

ከዲ/ን አብነት ተስፋ

የዚህ ኅብረት ምሳሌዎች

ይህን ህብረት ለመግለጽ በርካታ ቅዱሳን አበው የተለያዩ ምሳሌዎችን መስለዋል፡፡ ከእነዚህ መሃል ሁኔታውን ይበልጥ የሚገልጡት ሁለቱ ናቸው፡፡

ሀ) በሰው አካላት

ይህ ሀሳብ በተለይ የቅዱስ ጳውሎስ መለያ ነው፡፡ ከማንም በላይ ይህን ምሳሌ የቤተ ክርስቲያንን ህብረት ለመግለጽ የተጠቀመበት እርሱ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሰውነታችን የተለያየ ተግባር ያላቸው የተለያዩ  ክፍሎች አሉት፡፡ አንዱም የሌላው ተግባር ተክቶ ወይም ደርቦ መስራት አይችልም፡፡ አይን ማየት እንጂ መስማት ወይም መዳሰስ አይችልም፡፡ ጆሮም እንደዛው፡፡ ይሁን እንጂ አንዱ ሌላኛውን በጣም ይፈልገዋል፡፡ ዓይን ብቻውን አንድን ሰውን ሙሉ ማድረግ አይችልም፡፡ አንድ ሌላ የሰውነት አካል ቢጎድል ‹‹አካለ ጎደሎ›› ይባላል እንጂ ሙሉ ሰው አይባልም፡፡ እንደዛው ሁሉ በቤተ ክርስቲን ውስጥ ሁላችንም የአካል ብልቶች ነን፡፡ ስለዚህ አካል አንድ ሲሆን ብዙ ብልቶቸ እንዳሉት ሁሉ ኅብረቱም አንድ ሲሆን ነገር ግን ብዙ  አባላት አሉት፡፡ የሰውነት ብልቶች በፍጹም ኅብረት እና አንድነት አንድ ሙሉ የሆነ ሰውን እንደሚፈጥሩ ፍጹም የምእመናን ኅብረትም ቤተ ክርስቲያንን ይፈጥራል፡፡

        በዚህ ኅብረት ውስጥ ስንኖር ‹‹አይሁድም ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን  ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናል፡፡ (1ቆሮ 12፡13) ይህም ማለት ከሰሜንም እንሁን ከምሥራቅ፤ ብሔራችን ከየትም ይሁን ከየት ሁላችንም በአንዱ ክርስቶስ አንድ ነን፡፡ በሰውነታችን ደካማ የሚመስሉ የኣካል ክፍላት ሁሉ ጠቃሚ እነደሆኑ በዚሁ ኅብረት ውስጥም በእምነትና በምግባር ደካማ የሚመስሉ የኅብረቱ አባላትም አስፈላጊ ናቸው፡፡ በእምነት የበረታው በእምነቱ የደከመውን የሚያከብርበት፣ የሚራራበት ኅብረት እንጂ የሚያንቋሽሽበት፣ የሚዘባበትበት ኅብረት የለንም (ሊኖረንም አይገባም)፡፡ በዚህ ኅብረት ውስጥ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አይሁዳዊ ወይም ግሪካዊ የለም፡፡ ወንድም ወይም ሴትም የለም ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ፍጥረት ናችሁ፡፡ (ገላ 3፡27)›› እንዳለው ይህ ኅብረት ለበቁት ሰዎች የጾታን ልዩነትን እንኳን የሚያዘነጋ ኅብረት ነው፡፡ ይህም በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዛሙርት ሕይወት ውስጥ ተገልጧል፡፡

ለ) ቤተ-ሰብአዊ ሕይወት

        ቅዱስ አግናጥዮስ እንደሚለው ከሆነ ደግሞ ይህ ኅብረት ቤተ ሰብዓዊ ኅብረት ይመስላል፡፡ ቤተ ሰብእ  በአባት እና እናት መሪነት ልጆችን በፍቅር እና በእንክብካቤ አቅፎ ይይዛል፡፡ የቤተ ሰብኡ መሪ አባት ልጆች በምግባር እና በእምነት ታንጸው ከመልካም ስብዕና ይደርሱ ዘንድ መንገዳቸውን በተግሳጽ እና በምክር ይመራል፡፡ ስለዚህ ዘወትርም ቤተ ሰብኡን በማእድ ዙሪያ ይሰበስባል፡፡ ስጋዊ እና መንፈሳዊ ማእድ(ቃለ እግዚአብሔርን) ያቀርባል፡፡ መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለሟሟላት ዘወትር ይታትራል፡፡ እንደዛው ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ውስጥም እንደ አባት በመንጋው ላይ እረኛ ተደርገው የተሾሙ ካህናት አባቶች አሉ፡፡ ስለኅብረቱ አባላት መንፈሳዊ ሕይወት ማደግ አብዝተው ይጨነቃሉ፤ ነፍሱን ከክብር ስፍራ በዳግም ለማቆም በስብከት እና በንሰሃ ለማደስ ይተጋሉ፡፡ ከዚያም በላይ ደግሞ ምእመናንን ለሰማያዊ ማእድ በቅዱሱ ቁርባን ዙሪያ ይሰበስባሉ፡፡ እንደ አንድ ቤተ ሰብአም ከዚህ ክቡር ማእድ በጋራ ይቃደማሉ፡፡ ይህ ከምንም በላይ አንድ ቤተ ሰብአ ለመሆናችን ማሳያ ነው፡፡ ስለዚህ ንዋይ ኅሩይ ጳውሎስ ‹‹አንድ እንጀራ ስለ ሆነ፤ እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን፤ ሁላችን ያን አንድ እንጀራ እንካፈላለንና፡፡ (1ቆሮ 10፡11)›› አለ፡፡  ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊ ሕይወት ቤተ ሰብአዊ ሕይወት ነው፡፡

ይህ ክርስቲያናዊ ኅብረት በእኛ ዘመንስ

ከዘመነ ሐዋርያት አንስቶ ለበርካታ ዘመን የነበረችው ቤተ ክርስቲያን ይህን መሠረታዊ የኑሮ እና የአምልኮ መርህ የምትከተል ነበረች፡፡ ይቺ ኅብረት-ቤተ ክርስቲያን በተለይ በዘመነ ሐዋርያት ገና ተወልዳ ማደግ በጀመረችበት ጊዜ ይህ ቤተ ሰብአዊ ኑሮ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ያበበት ጊዜ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩት የመጀሪያዎቹ ክርስቲያኖች ሀብት ንብረታቸውም ጭምር እንኳን ሽጠው በሐዋርያት እግር ስር እያኖሩ ‹‹ይሄ የእኔ ይሄ ደግሞ ያንተ›› የሚባል ነገር የሌለበት ፍጹም የሆነ ሕብረታዊ ሕይወት ነበራቸው፡፡ አይሁዶች እና የግሪክ ሰዎች መለያየት ሳይኖርባቸው ሁሉም ባንድነት በጋራ ሥጋዊ ማእድ ዙሪያ ይታደሙ ነበር(ሐዋ 6፡1-6)፡፡ ለጸሎትም በአንድ ላይ  ይሰበሰቡም ነበር፡፡

        ከዚያም ከሐዋርያት በኋላ በተነሱ ክርስቲያኖች ዘመንም ይህ ቤተ ሰብአዊ እና ኅብረታዊ ሕይወት እንደቀጠለ ነበር፡፡ ሁሉም የኅብረቱ አባል በጋራ የአምልኮ ተግባራት ላይ መሳተፍ እና ከቅዱስ ሥጋውና ደሙ መቀበል ለሁሉም የኅብረቱ አባላት ግዴታ ነበር፡፡ በቅዳሴ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን አንድ ምዕመን ካልተገኘ አንዳች ክፉ ነገር አጋጥሞት ነው ተብሎ ስለሚታሰብ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ወይም መልእክተኛ ይላክበት ነበር፡፡ ስለዚህም ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው ቅዳሴያችን ‹‹አመቦ ብእሲ እምእመናን . . . ከምእመናን በቅዳሴ ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲን የገባ ክቡራት የሚኆኑ ቅዱሳት መጻሕፍትን የማይሰማ የቅዳሴው ጸሎት እስከሚፈጸም የማይታገሥ ሥጋውን ደሙን የማይቀበል ሰው ቢኖር ከቤተ ክርስቲያን ይውጣ፡፡ ነፍስን እና ሥጋን በሚገዛ በሰማያዊ ንጉስ ፊት መቆምን አቃሏልና፡፡››

        በእኛ ዘመን ግን ለቤተ ክርስቲያን ያለን ግንዛቤ በተግባር ሲመዘን ከህንፃ ያለፈ አይደለም፡፡ በዚህ ጽሑፍ በስፋት ለማተት እንደተሞከረው ቤተ ክርስቲያንን ለመመስረት ህንጻ በቂ አይደለም፡፡ ወይም ወሳኝ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ህንፃ ባልተገነባበት ዘመን ራሱ ነበረች፡፡ ዋናው ህልውናዋን የሚመወስነው ኅብረታዊ ማንነቷ ነው፡፡ ስለዚህ በህሊናም በተግባርም ለኅብረታዊ ተግባራቶቿ ከፍተኛ ቦታ ልንሰጥ ይገባል፡፡ እነዚህም የጋራ የአምልኮ ስርዓቶቿ ናቸው፡፡ የዚህም አውራው ስርዓተ ቅዳሴ ነው፡፡

        በመሆኑም በዚህ መሠረት በዚህ ዘመን ያለን ምእመናን በሁለት ተከፍለን ልንታይ እንችላለን፡፡ ከሥላሴ ልጅነትን ያለን እና በኅብረቱ ውስጥ ቀጥተኛ አባል የሆንን እና ከሥላሴ ልጅነት ቢኖረንም በአንገታችን ካሰርነው መስቀል ውጪ የኅብረቱ አባል ያልሆንን ተብለን ልንከፈል እንችላለን፡፡ ክርስትና  ኅብረታዊ ናት፡፡ ስለዚህ ሁሉም ምእመን በኅብረታዊ አገልግሎቶች ውስጥ መሳተፍ አለባቸው፡፡ ይህም ከቤተ ክርስቲያን ጋር ቀጥተኛ ግንኑነት እንዳለ ማሳያ ናቸው፡፡

        አንድ/አንዲት ምእመን ከቤተ ጋር ቀጥተኛ ተሳትፎ አላው የሚባለው ቢያንስ በሁለት ነገር ይለካል፡፡ የመጀመሪያው በኅብረታዊ ስርዓተ አምልኮ በተለይም በቅዳሴው ላይ ባለው ተሳትፎ ነው፡፡ ስለዚህም ሠለስቱ ምዕት በህንፃ መነኮሳት ላይ አበክረው ‹‹ወበጽብሐ ዕለተ እሁድ አሌሊ ገይሰ ኀበ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት በጽባህ . . . እሁድ ቀን በጧት እጅግ ማልደህ ከሌሊቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒድ፡፡ ስትሔድም ልቡናህን በማባከን ወዲያና ወዲህ አትይ፡፡ በቅዳሴም ጊዜ ሕማሙን ሞቱን ትንሳኤውን እያሰብክ በፍጹም ፍርሃት ቁም (ሃ.አ ም 20፡22)›› ሲሉ ያዙናል፡፡ በዚህም በኅብረቱ ሙሉ ተሳታፊነታችን ይገለጥ ዘንድ ከታላቁ ምሥጢር ከቅዱስ ስጋውና ደሙ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህም ነው መጽሐፍ ሲቻለው ከቅዱስ ቁርባኑ የማይቀበለውን ሰው ‹‹መሢሐዊ ዘኢይነሥዕ እምቁርባን እነዘ ይትከሃሎ ይከውን ከመ ዘኢተጠምቀ እምድኅረ ተጠምቀ . . . ክርስቶሳዊ ሲቻለው ከቁርባኑ ካልተቀበለ ከተጠምቆ በኋላ እንዳልተጠመቀ ይሆናል›› የሚለን፡፡  

        ዳግማኛም ከቤተ ክርስስቲያን ጋር ያለን ቀጥተኛ ግኑኘት አለን እንዲባል የንሰሃ አባት ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡ ንሰሃ አባቶች ስንቸገር የምናማክራቸው፤ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን መለምለም ምክርን የምንጠጣባቸው ምኝጮቻችን ናቸው፡፡ ለእነሱ ስለመንፈሳዊ ነገር ብቻ ሳይሆን አንዳንዴም የዓለማዊ ስራዎቻችንን ወይም ጉዳዮቻችንን ጭምር እናማክራቸዋለን፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያንን በሕይወታችን ውስጥ ለሰጠናት ድርሻ ማሳያ ናቸው፡፡(በትረ ሃይማት) ዳግመኛው ኅብረታዊነታችንን የሚጠብቁ እረኞች ናቸው፡፡ ማለትም በኅብረታዊ ስርዓቶች ላይ ያለንን ተሳትፎ ይቆጣጠራሉ፤ ያስተካክላሉ፡፡ ስለዚህ አንድ ኦርቶዶክሳዊ ለተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት በእጅጉ ያስፈልጉታል፡፡

ስንጠቀልለው

        ክርስትና በኅብረት እና በአንድነት በሚደረግ አገልግሎት የሚገለጥ ነው፡፡ በዚህ ኅብረት ውስጥ ከክርስቶስ ጋር በቅዱሳት ምሥጢራት እንዋሐዳለን፡፡ ከቅዱሳን ጋር በሃይማኖት ተመሳስለን ለምስጋና እንቆማለን፡፡ ስለዚህም ኅብረታዊነታችን አርስ በርስ ባለን ግንኙነት፤ በጋራ ስርዓቶቻችን ደግሞ ከቅድስት ሥላሴ  ያለን ግንኙነት፤ በንሰሃ አባቶቻችን ውስጥ ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያለን ቀጥተኛ ግንኙነት  ሊገለጥ ይገባል፡፡ ኅብረታዊነት በምእመናን እርስ በርስ ማለት ማኅበራዊ ግንኑነት(እንደ ጽዋ፣ ሰንበቴ. . ወዘተ) ባሉት አገልግሎቶቻችን ውስጥም ይገለጣል፡፡(የዚሁ መጽሔት ክፍል የሆነውን ማኅበራዊ አስተምህሮ የተሰኘውን የበረከት ጉዲሳን ጽሑፍ ይመልከቱ!!!) ጉዳዩ እጅግ በጣም ሰፊ እና ከዚህ በላይ ሊጻፍበት የሚገባ መሆኑ ይሰማኛል፡፡ ‹‹አብዝሆ ነገርሰ ሕማም ወገአር ውእቱ›› እንዲል በዚህ ልፈጽም፡፡ ለዛሬ ግን መሰነባበቻችንን የቤተ ክርስቲያናችንን የቅዳሴ ጸሎት ማረግን ወደድን፡፡ ‹‹በኩሉ ልብ ናስተብቁኦ ለእግዚአብሔር አምላክነ ኅብረተ መንፈስ ቅሱስ ሰናየ ከመ ይጸግወነ››

ዋቢ መጽሐፍቶቼ

1 አባ ጎርጎርዮስ፣ 1986 አዲስ አበባ፣ የኢትዮጽያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣

2 አባ ጎርጎርዮስ፣ 1978 አዲስ አበባ፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፣

3 – – – — ፣ መጽሐፈ ቅዳሴ አንድምታ፣ 2010 አዲስ አባባ፣ ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት

4  – – – -፣ ወንጌል ቅዱስ አንድምታ፣ 1995 አዲስ አባባ፣ ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት

5 – – – – ፣ የቅዱስ ጳውሎስ መጽሐፍ ንባቡ ከትርጓሜው፣ 2008 አዲስ አባባ፣ ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት

6 ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳስ ዘጎንደር ፣ መጽሐፍተ ሠለስቱ ሃዲሳት፣ 1989 አዲስ አባባ፣ ትንሳኤ

7. መጋቤ ሐዲስ ፍቅረ ማርያም    ፣ 2008፣ ሃይማተ አበው አንድምታ፣

8 ቀሲስ መዝገቡ ካሳ (ዶ/ር)፣ በትረ ሃይማኖት፣ 2010 አዲስ አበባ፣ ፋር ኢስት ትሬዲንግ ኃላ.የተ.የግ.ማኅበር

9 Philip Schaaf, The Ante- Nicene Fathers vol 1 & 2, American re print of the Edinburg edition soft copy

10 Vladmir losky, In the image and likeness of God, St Vladmir seminary press New York

11 Georges Florovsky, 1972, Bible, church & Tradition, Norland Publishin Campany

12 Thomas Hopko, —-, Ministry And The Unity Of The Church: An Eastern Orthodox View,

13 Fr Paul Verges, 2011, The Nature of The Church,

14. John Mayendorff, 2014, On The Unity Of The Church, International journal of Orthodox Theology

15. John Julion, 2018, The Inward Being and The Out ward Identity: The Orthodox Church in 21st century, special issue published online

16. Fr Thomas Hopko, The one True Church, Ancient Faith radio podcast

share this:

Leave a Reply