የቤተ ክርስቲያን ኅብረት ከትናንት እስከ ዛሬ ክፍል 2

የቤተ ክርስቲያን ኅብረት ከትናንት እስከ ዛሬ ክፍል 2

ከዲ/ን አብነት ተስፉ

ታዲያ ኩላዊነት ማለት ምን ማለት ነው?

ዓለም አቀፋዊነት የኩላዊነትን ትርጉም የሚጋራ ነገር ግን የማይተካ ቃል ነው፡፡ ኹለንተናዊነት የኩላዊነት ውጤት ነው እንጂ ኹለንተናዊነት የኩላዊነት መንስዔ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲን ዓለም ዓቀፋዊ ሆና ኩላዊት ላትሆን ትችላለች፡፡ ነገር ግን አለም አቀፋዊ ሳትሆን ግን ኩላዊት የነበረባቸው ጊዜ ነበር፡፡ ስለዚህ ገና በዓለም ባልተዳረሰሰችበት በዚያ በጥንት ዘመን የነበሩ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ቃሉን ሲጠቀሙት ዓለም አቀፋዊነት ለመግለጽ አልነበረም፡፡

ኩላዊነት በዚህ በሐዲሲቱ ስብስብ መሃል ያለ ውስጣዊ አንድነት እና መተባበርን (concrete oneness in thought and feeling) የሚገልጽ ቃል ነው፡፡ ኩላዊነት የስብስቡ አባላት የእምነታቸውን መገለጫ በሕብረታዊ ስርዓተ አምልኮ ውስጥ የሚገልጡበት አንድነት ነው፡፡ ስለዚህም በአንድነት ተሰባስበው ‹‹ነአምን በአሐዱ አምላክ ገባሬ ኩሉ ፍጥረት አብ፤ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመደኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ . . . . ›› ብለው በኅብረት ይገልጣሉ፡፡ በኅብረት ሆነው የክርስቶስን ሞቱን እና ትንሳኤውን ይናገራሉ፡፡ እንዲህ ይላሉ ‹‹ንዜኑ ሞተከ እግዚኦ ወትንሳኤከ ቅድስት . . . ሞትህን እንናገራለን፣ ቅድስት የምትሆን ትንሳኤህንም . . . ›› በሕይወታቸው ውስጥም የተፈጠሩለትን ዓላማ ክርስቶስን ለመምሰል በሚያደርጉት ጉዞ እርስ በርሳቸውም፤ ከንሰሃ አባቶች እና ከቤተ ክርስቲያን ራስ ከክርስቶስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚገልጥ ነው፡፡

ዳግመኛም ቃሉ ይህን ህብረት በአንድ አይነት አስተሳሰብ እና የሕይወት መመሪያ(principle) መሠረት አድርገው ከተቋቋሙ ሌሎች ዓለማዊ ስብስቦች የሚለይ ነው፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ኩላዊት የምትሰኘው የክርስቶስ አካሉ ስለሆነች ነው፡፡ ይህን ያገኘችው ደግሞ ከሰማይ ደጅ ጋር የሚያገናኛትን ምሥጢራት ስለምትፈጽም ነው፡፡ በጥምቀቱ የሥላሴ ልጅ ትባላለች፤ በቅዱስ ቁርባን ከክርስቶስ ጋር ትዋሃዳለች ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ‹‹ቤተ ክርስቲያን የሚያሰኘው ቅዱስ ቁርባን ነው፡፡ ምክንያቱም ፍጹም አካሉ ነውና ክርስቶስ ለመገኘቱ ፍጹም ማሳያ ነው፡፤ ቅዱስ ፖሊካርፐስ እንደሚለው ደግሞ ክርስቶስ ባለበት ቦታ ኩላዊት የሆነች ቤተ ክርስቲያን አለች (wherever Jesus Christ is, there is the Catholic Church.) ስለዚህም በእነዚህ እና በሌሎችም ምሥጢራት ከመለኮቱ የጸጋው ሙላት ተካፋይ ትሆናለች፡፡ በመሆኑም ከሥጋ ስብስቦች ከእድር እና ከእቁብ ከፍ ትላለች፡፡ ስለዚህም ኩላዊት ትባላለች፡፡

ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን አደገች፤ ሰፋች የሚባለው ሀገር አቋርጣ፣ ባህር ተሻግራ ስለ ተመሰረተች አይደለም፡፡ የቤተ ክርስቲያን እድገት መጀመሪያ የሚለካው በውስጣዊ አንድነቷ ነው፡፡ ብዙ ምእመናን በጋራ አምልኮ ስርዓት ላይ በማይሳተፉበት ሁኔታ፤ በመንፈሳዊ ሕይወትም እርስ በርስ በማይመሳሰሉበት (በማይተባበሩበት) ሁኔታ በቁጥር ብቻ ስለበዛች ‹‹ቤተ ክርስቲያን አድጋለች፣ ሰፍታለች›› አያሰኝም፡፡ የቤተ ክርስቲያን እድገት መለኪያ የብዙ ምእመናን በአንድነት ለሰማያዊ አምልኮ መሰየማቸው፤ የብዙ ምእመናን በንሰሃ ሕይወት እራሳቸውን አድሰው ፍጹም ክርስቶሳዊ በመሆናቸው፤ በእየእለት ከክርስትና ቅጽር ውጪ ባለው የማኅበራዊ ሕይወታቸው ‹‹እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ የራሱን ጥቅም አያስብ›› በሚለው አምላካዊ ቃል መሠረት መተባባበር በመቻላቸው የሚለካ ነው፡፡ ስለዚህም ኩላዊነት የቤተ ክርስቲያንን እድገት የምንሰፍርበት መስፈሪያ ነው፡፡ በዚህ መስፈሪያ ስንለካ እውን የእኛ ቤተ ክርስቲያን እድገት ምን ያህል ነው?

በዚህ ኅብረት ውስጥ ከማን ጋር ነው ኅብረት የምንፈጥረው?

ወደ ክርስትና ሰፊ አዳራሽ የምንገባ እኛ ምእመናን ከሁሉ አስቀድመን በምሥጢራት ቀድመን የምናገኘው ከዚያም ልዩ ኅብረት የምንፈጥረው ከክርስቶስ ጋር ነው፡፡ ጳውሎስ ‹‹የተጠመቃችሁ እናንተ ክርስቶስን ለብሳችኋል (ገላ 3፡27)›› እንዳለ በሐዲስ ልደት በጥምቀት ስንወለድ ለሰማያዊው ሰርግ የምንለብሰው ንጹህ ልብሳችን ክርስቶስ ነው፡፡ እሱን የለብሱ በሙሉ በኋላ በዳግም  ምጽአት ‹‹የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ (ማቴ 22፡12›› ተብለን ከመንግስተ ሰማያት ድግስ እንወጣለን፡፡ በደብረ ጽዮን ከሚደረገው ምስሀ እንከለከላን፡፡ ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ ገሃነመ እሳትም አንወርዳለን፡፡

ስለዚህ እርሱን ክርስቶስን በለበሰች በዚህ ስብስብ ውስጥ ክርስቶስ ‹‹ራሳችን›› ነው፡፡ ንዋይ ኅሩይ ብጹዕ ጳውሎስ ‹‹እርሷም [ቤተ ክርስቲያን] አካሉና ሁሉን በሁሉ የሚሞላ የእርሱ ሙላቱ ናት፡፡ ኤፌ 1፡23›› እንዳለ የዚህ ኅብረት አካል በመሆን ከእኛ ጋር አንድ ነው፡፡ ከአካላትም ደግሞ ለዚህ ኅብረት ክርስቶስ ራሷ ነው፡፡ ‹‹ርዕስ – ራስ›› ሕይወታችን እንደሚመራ፣ አካሄዳችንን እንደሚወስን እነደዛው ሁሉ ክርስቶስ የዚህን ማኅበር ህልውና የሚወስን፣ አካሄዷን የሚወስን አቅጣጫ ጠቋሚያችን ነው፡፡ እርሱም ‹‹ወናሁ አነ ምስሌክሙ በኩሉ መዋዕል እስከ ኅልቀተ ዓለም . . . እነሆ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋራ ነኝ (ማቴ 28፡19) ሲል ቃል ኪዳኑን ትቶልን አልፏል፡፡ እኛም እንደ ተቀረው አካል ክፍሎች ከእርሱ ጋር ፍጹም አንድነት እና ግንኙነት አለን፡፡ በበላነው ሥጋው በጠጣነው ደሙ በማይበጠስ ገመድ ተሳስረናል፡፡ ሥጋው ከሥጋችን ፣ ደሙ ከደማችን ተዋህዶ ክርስቶስ በሁላችን አካል ክፍሎቹ ውስጥ ይኖራል፡፡

በቀድሞ ጊዜ እስራኤል ከባርነት ምድር ከግብጽ ለመውጣት ከመሪያቸው ሙሴ ጋር በደመና እና በባሕር ተባበሩ (1 ቆሮ 10፡2)፡፡ በሐዲስ ኪዳን ለመንግስተ ሰማያት መሪያችን(ራስ) ከሚሆነን ከክርስቶስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ተባበርን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀበራችሁ፣ በጥምቀትም ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሳችሁ፡፡ (ቆላ 2፡12) እንዳለን ስለዚህ ትብብራችን (ሞቱን በሚመስል ሞት በጥምቀቱ ስለተባበርን) በዳግም ምጽዓቱ ትንሳኤውን በሚመስል ትንሳኤ እንተባበራለን(ሮሜ 6፡4)፡፡ ስለዚህ በዚህ ኅብረት ውስጥ ዋናው ሕብረታችን ከክርስቶስ ጋር ነው፡፡

ዳግመኛው በዚህ ኅብረት ውስጥ በብሉይ ኪዳን የሚኖሩ አባቶችን እናገኛለን፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹በነቢያት እና በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል እንዳለ የዚህ ኅብረት መሠረት ‹‹ይመጣል . . . ይወለዳል›› የሚለው የነቢያት ትንቢትና ‹‹የሞተው ተነስቷል›› የሚለው የሐዋርያት ስብከት ነው፡፡ ስለዚህ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘየዓቢ እንደሚለው ‹‹ከሙሴ ህግ በፊት የነበሩ በጸጋ የሚኖሩ እነዚህ ሁሉ የቤተ ክርስቲያን አባል ናቸው፡፡›› ምክንያቱም አውግስጢኖስ እንደሚለው እኛ መጣ ብለን የምናምነውን እነሱ ይመጣል ብለው ያምናሉና እነሱም ክርስቶሳውያን ናቸው፡፡ ዳግመኛም እነሱም ስለጸኑበት ተስፋቸው እኛም ስለጠበቅነው ጸጋችን አንድ አይነት ሽልማት መንግስተ ሰማይን የምንቀበል ነንና ሁለታችንም አንድ ማኅበርተኞች ነን፡፡ ስለሆነም እነ አብርሃም፣ ሙሴ፣ ነቢያቶቹም ሁሉ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡

እንዲሁም በዚህ ኅብረት ውስጥ የሰማይ መላእክትን እናገኛቸዋለን፡፡ እነሱም ከእኛ ጋር ፍጹም ኅብረት አላቸው፡፡ ምክንያቱም እነሱ 24 ሰዓት ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ›› እያሉ የሚያመሰግኑትን ነው እኛም ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር፣ ቅዱስ ሃያል፣ ቅዱስ ህያው ዘኢይመውት›› ብለን የምናመሰግነው፡፡ እነሱ በሰማያዊ አዳራሽ ቆመው እየፈሩ የሚያጥኑትን አምላክ ነው እኛም ‹‹ንሰግድ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ›› እያለን ስለ ክብሩ ብዛት ማዕጠንት የምናቀርበው፡፡ ስለዚህም ሃይማኖታችን በዓለመ መላእክት ‹‹ንቁም በበህላዌነ እስከነአምሮ ለአምላክነ . . . አምላካችንን እስክናውቀው በያለንበት ጸንተን እንቁም››(መጽሐፈ አክሲማሮስ) ባሉ ጊዜም የነበረችዋ የመላእክት ሃይማኖት ነች፡፡ እኛም የምናመልከው እነርሱ ‹‹ለይኩን ብርሃነ . . . ብርሃን ይሁን›› ብሎ በተገለጸላቸው ጊዜ ያመሰገኑትን አምላክ ነው፡፡ ስለዚህ መላእክም ክርስቲያኖች ናቸው፡፡

በመሆኑም በዚህ ኅብረት ውስጥ መላእክት ዘርፈ ብዙ ድርሻ አላቸው፡፡ በመንገዳችን ሁሉ ከክፉ የሚጠብቁን ጠባቂዎቻችን ናቸው መዝ90÷11 ፡፡ ክርስቶስን በመምሰል ሂደት ውስጥ መዳናችና የሚያግዙ ረቂቃን መናፍስት ናቸው ዕብ1÷14 ፡፡ ወደ እግዚአብሔር በመመለሳችን – በንሰሃችን ታላቅ ደስታን የሚደርጉ ቀንደኛ የኅብረቱ አባል ናቸው ሉቃ15÷10 ፡፡ ዳግመኛም በአጸደ ቤተ ክርስቲያን ተገኝተን የምንለምነውን ልመና ወደ ፈጣሪ የሚያደርሱ ተላላኪዎቻችንም ናቸው ራእ8÷3 ፡፡ እንዲሁም ‹‹ኅብስተ መላእክቲሁ በልዑ እጓለ እመ ሕያው . . . የመላእክን እንጀራ የሰው ልጆች በሉ መዝ 77÷25 ›› ተብሎ እኛ ለመላእክት ምግብ ከሚሆናቸው ምስጋና መሳተፋችን ተነግሮልናል፡፡ ስለዚህ በዚህ ኅብረት ውስጥ ከመላእክት ጋር በሰማዩ ዙፋን ዙሪያ ለሰማያዊ ህብስተ መና- ምስጋና አብረን የምንቀመጥ አንድ ቤተሰብ ነን፡፡

በተጨማሪ በዚህ ኅብረት ውስጥ አረፍተ ዘመን የገታቸው፣ ነገር ግን ‹‹መልካሙን ገድል ተጋድያለሁ፤ ሩጫዬን ጨርሻለሁ›› ብለው በክብር ዓለምን አሸንፈው የሞቱ ሰዎች ይገኛሉ፡፡ እነሱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ህያው ናቸው፡፡ ‹‹የጻድቅ መታሰቢያ ለዘለዓለም ነው›› እንደተባለ ዘለዓለማዊ መታሰቢያ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አላቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እግዚአብሔር ሰንበቱን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰነውንም ነገር ስለሚመርጡ ሰዎች ‹‹በቤቴ እና በቅጥሬ ውስጥ የማይጠፋ መታቢያ ስም እሰጣቸዋለሁ፡፡ (ኢሳ 56፡4-6)›› ሲል ቃል በገባው መሠረት የክርስቶስ ስጋና ደም የሚከብርበት፣ ዘላለማዊ ስሙ የተጻፈበትን ጽላቱን በስማቸው ሰይማ ህያው ታደርጋቸዋለች፡፡ ዘወትር ማለዳ ማለዳ ‹‹ወበዛቲ እለት አዕረፈ አባ እገሌ›› እያለች በስንክሳር ታሪካቸው ዘግባ፣ የምስጋናን አርኬ ደርሳ መታሰቢያቸውን ታደርጋለች፡፡ ከዚያም በላይ ደግሞ ስማቸው ጠርታ በረከታቸውን ትማልዳለች፡፡ ስለዚህ ሁሉም ዓለምን በድል የፈጸሙ ቅዱሳን በዚህ ኅብረት ውስጥ ሕያው ሆነው ከእኛም ጋር ፍጹም አንድነት አላቸው፡፡

share this:

Leave a Reply