ቤተ ክርስቲያንና ቄሣር

ቤተ ክርስቲያንና ቄሣር

(ሽራፊ ሐሳብ)

ዲ/ን ከሣቴብርሃን ገ/ኢየሱስ


መንደርደርያ

ቤተ-ክርስቲያን ሰማያዊ ሥርዓት የሚተገበርባት የሰማይ ደጅ ብትሆንም ምሥረታዋና እንቅስቃሴዋ በምድር ነውና ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም “ቄሣራዊ ኃይላት” ከሚሏቸው መኳንንተ ዓለም ጋር በታሪክ መድረክ መገናኘቷ አልቀረም፡፡

ይኼም በወንጌል መስፋፋትና በምዕመናን አንድነት፣በሰማዕታት ሕይወትና በሌሎች እልፍ የቤተክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ሠናይም ሆነ እኩይ አሻራውን ትቶ አልፏል፡፡  በሌላ ገጽ በመንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ ቤተ-ክርስቲያንና ልጆቿ ያሏቸው ዕይታና ተሳትፎ በአራት ነጥብ የተዘጋ ነው ወይስ እስከ ቀይ መስመሩ ድረስ መሄድ ይቻላል? የሚለው ጉዳይ ጎራ ለይቶ እያነታረከ ያለበት ወቅት ላይ በመሆኑ ብዥታዎችን በመጠኑ የማጥራት አላማ የሰነቀ አጠር ያለ ጽሑፍ አስፈልጓል፡፡

‹‹መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም›› (ማቴ. 19፡36)

ጌታችን በአውደ ምኵናን በጲላጦስ ፊት ቀርቦ ከተናገራቸው እጅግ ታላቅ ምሥጢርን ከያዙ ቃላት መካከል ‹‹መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም,,. የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ ቃል ውስጥ ጠቅላላ የክርስትናን ዓላማና ግብ እናገኝበታለን፡፡

እግዚአብሔር ንጉሥ ነው፡፡ ያውም አንጋሽ (የሚነግሥበት ሕዝብ) የማይፈልግ ‹‹ እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም›› ‹‹እግዚአብሔር ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነበር›› እንዲል (መዝ.74፥12)፡፡ ነገር ግን ምስጋናው በባሕርይው እንዳይቀር 22ቱን ሥነ ፍጥረታትና 20ውን ዓለማት ፈጥሮ ሁለቱን ለባውያን አመስጋኝ አድርጎ እንዳከበራቸው እንዲሁ ቅድመ ዓለም የነበረ የባሕርይ ንግሥናውን ለአዳም በጸጋ አደለውና በምድር ያሉትን ፍጥረታት ሁሉ እንዲገዛና ገነትንም እንዲጠብቅ ሥልጣን ሰጠው፡፡

ዳሩ ግን በአምላክነት ምኞት በሰማያዊው ዙፋን ለመቀመጥ ቅዠት አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ ቆርጦ ቢበላ የተሰጠውን ክብር አጣ፡፡ ንግሥናው ቀርቶ የዲያብሎስ ባርያ(ገብሩ ለዲያቢሎስ) ብሎ ፈርሞ ለ5500 ዘመን በእግረ አጋንንት ሲጠቀጠቅ ኖረ፡፡

ጥፋቱን የማይወድ አምላክ ግን ‹‹በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃለዕለት እትወለድ እም ወለተ ወለትከ›› ብሎ የሰጠውን የተስፋ ቃል እንዲፈጸም የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ ከሴት የተወለደ ልጁን ሰደደ፡፡ የመምጣቱም ዓላማ አዳምን ከነልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩና ንግሡ መመለስ ነው፡፡ ይኼም የሚፈጸም በመስቀል ሞት ነውና ራሱን የሰው ልጅ ብሎ እየጠራ  የመጣው አምላክ ራሱን በመስቀል ሞቱ በሚነግሡና በሚከብሩ ምዕመናንቦታ አግብቶ ሞቱን ክብር ብሎ ጠራው። በመስቀልም እነግሣለሁ አለ፡፡ መስቀሉም ዙፋኑ፣የእሾህ አክሊል ዘውዱ፣ቀይ ግምጃ ልብሰ መንግሥቱ ፣በዘንግ መመታት በትረ መንግሥቱ ሆነውለት ነገሠ፡፡

በዚህም መንግሥተ እግዚአብሔርን መሠረተ፡፡ ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ በ40 በ80 ቀን ተጠምቆ የመንግሥት ልጅነት ያገኘ ደግሞ ወራሽ ይሆናል፡፡(ገላ.4፥7) ይህቺውም ውርስ ከክርስቶስ ጋር በአንድነት ነግሠን የምንኖርበት መንግሥተ ሰማይ ናት፡፡

ስለሆነም ጌታ በርዕሱ የተቀመጠውን ኃይለ ቃል የተናገረው በእሱ አንጻር ስለ ምዕመናን ነው። ለክርስቲያን መንግሥት ከዚህ ዓለም አይደለችም። የክርስቲያን ሃገሩ በሰማይ ነው።(ፊልጵ.3፥20)ባንዲራው መስቀል ነው። ተስፋውም መንግሥተ ሰማይ ነው፡፡ቤተ-ክርስቲያንም የሰማያዊው መንግሥት የምድር ቆንስላ ጽ/ቤት ናት ፡፡ ክርስቲያኖች ዓለም እንደ ኪራይ ቤታቸው ናት፡፡ ስለሆነም ክርስቲያኖች እንደያዕቆብ “የእንግድነቴ ዘመን ይኼን ያህል ነው” እያሉ እድሜያቸውን የሚቆጥሩ ፤ እንደ ዳዊትም“በምድር ላይ መጻተኛ ነኝ፥ እንደ አባቶችም እንግዳ ነኝ።”የሚሉ ናቸው፡፡(ዘፍ.47፥9 , መዝ.39፥12) ሊሄዱም ከክርስቶስ ጋር ሲኖሩም እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ይናፍቃሉ፡፡

ታዲያ ክርስቲያን ከዚህ ዓለም መኳንንት ጋር ያለው ግንኙነት ምን ይምሰል?

ነገር ግን በኪራይ ቤት ያለ ሰው የራሱን ቤት ቀልሶ መኖር እየናፈቀ ከሚኖርበት ጊዜያዊ ቤት ባለቤት(አከራይ) ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠር እንዳለበት እንዲሁ ምንም ሃገርና መንግሥታቸው በሰማይ ቢሆን የተጠለሉት በዓለም ነውና ለዓለም አስተዳዳሪዎች የሚገባውን ፣ የሚጠበቅባቸውንም ግዴታ እየተወጡ እንዲኖሩ ታዘዋል፡፡ አንድም ነገሥታት የሚነግሡ በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ ሠናይም ይሁኑ እኩይ፡፡

በእርግጥ እግዚአብሔር ወዶ ለሕዝብ ጥቅም የሚያነግሣቸው ‹‹ለእስራኤል ጥቅም የነገሠ ዳዊት›› ተብሎ የተነገረለት ዓይነት ንጉሥ እንደሚያስነሣ ሁሉ ‹‹ወአንገሦሙ ብእሴ መዳልወ በእንተ እኩይ ሕዝብ››እንዲል ስለ ሕዝቡ ጠማምነትና ጩኸት ክፉ ንጉሥ ሊያነግሥ ይችላል፡፡ የወደደውም ይሁን የፈረደው ቢሆንም ግን ቅሉ ከጌታ ፈቃድ ውጭ በዙፋን የሚቀመጥ የለም፡፡ ለዚያ ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ነፍስ ሁሉ በበላይ ባሉት ባለሥልጣኖች ይገዛ ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና ያሉትም ባለሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው ስለዚህ ባለሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል፡፡ የሚቃወሙት በራሳቸው ላይ ፍድን ይቀበላሉ›› (ሮሜ 13፡1-2) በማለት የተናገረው፡፡ቅዱስ ጴጥሮስም እንዲህ ብሏል;-‹‹ስለ ጌታ ብላችሁ ለሰው ሥርዓት ሁሉ ተገዙለንጉሥም ቢሆን ከሁሉ በላይ ነውና፡፡›› (1ኛ ጴጥ 2፡13)

ክብር ይግባውና አምላካችንም ግብር እንዲገብር በተጠየቀ ጊዜ የሰማያዊ መንግሥት ልጆች ከግብር ነጻ እንደሆኑ በምሥጢር ካስረዳ በኋላ ላለማሰናከል ግን ቅዱስ ጴጥሮስን ከባሕር ዓሣየሚያገኘውን ሁለት ዲናር ስለጌታ እና ስለ እርሱ እንዲከፍል ነግሮታል፡፡(ማቴ.17፥27)

ስለዚህ ክርስቲያኖች በዚህ አብነት ለነገሥታትና ለመኳንት እንደሚገባ አክብሮት ሲሰጡ የሚጠበቅባቸውንም ግብር ሲከፍሉ ኖረዋል፡፡አንዳንዶቹም በመንግሥት ሥልጣን ላይ ሳይቀር ተቀምጠው ሃገራቸውን አገልግለዋል፡፡ ምክንያቱም ከመሠረታዊ የክርስትና ዓላማ  ጋር እስካልተጋጨ ድረስ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ መሳተፍ የተነቀፈ አይደለምና ነው፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ ቀራጮች መጥተው ሲጠይቁት ‹‹ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ ›› አለ እንጂ ቀራጭነትን ተዉ” ብሎ አልተናገራቸውም፡፡ ወታደሮችም መጥተው ምን እናድርግ ባሉት ጊዜ ‹‹በማንም ግፍ አትሥሩማንንም በሐሰት አትክሰሱደመወዛችሁም ይብቃችሁ›› አለ እንጂ የመንግሥት ወታደር መሆን የለባችሁም አላላቸውም፡፡(ሉቃ.3፥12-14)

ጉምቱዎቹ ሰማዕታት እነ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ቅዱስ መርቆሬዎስና ቅዱስ ፊቅጦር በውትድርና አገልግለዋል፡፡ እነ ቅዱስ አምብሮስ የሚላን ሹማምንት ነበሩ፡፡በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንኳ ታላላቅ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ያገለገሉ ብዙዎች የቤተክህነት ሰዎች ናቸው፡፡ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ መርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስ፣ተክለጻድቅ መኵሪያ እያሉ ብዙመዘርዘር ይቻላል፡፡

ዳሩ ግን ነገሥታት<<kyros kysarios>>‘ቄሣር ጌታ ነው’<<theosos kysarios>>‘ቄሣር አምላክ ነው’ ‹‹አምልኩኝ ፥ለሥዕሌም ዕጠኑ” ያሉ ጊዜ ቀይ መስመሩ ታልፏልና ‹‹እኔ ክርስቲያን ነኝ፣የማመልከው ክርስቶስን ነው የምሰግደውም ለእርሱ ብቻ ነው›› ብሎ መከራን መቀበል የግድ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትም ሰማዕታት ያደረጉት ይኼንኑ ነው፡፡

ስለዚህ ዛሬም አንድ የቤተክርስቲያን ሰው የመንግሥት ሥልጣን ላይ ሲገኝ “እንዴት እርሱ መምህር፣አገልጋይ ሆኖ እዚያ ተገኘ?” ሳይሆን መባል ያለበት“ቀይ መስመሩ ሲታለፍ ምን አደረገ?” የሚል ጥያቄ ነው መሰንዘር ያለበት፡፡

ቄሣር ቤተክርስቲያንን በምን መልኩ ተጽዕኖ ሊያሳድርባት ይችላል?

ቄሣራዊ ኃይል ቤተክርስቲያን ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አዎንታዊና አሉታዊ ብለን በደምሳሳው ብንከፋፍለው የሚያመዝነው ወደ አሉታው ነው፡፡

አሉታዊ ተጽዕኖው ዳግም በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና የተገለጠ ነው፡፡ ተቀዳሚውና ዋነኛው በተለይም በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ምዕተ ዓመታት የተከሰተው  አውዳሚ ተጽዕኖው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተዘረዘረው የነገሥታቱ የመመለክ ፍላጎትና የክርስቲያኖች እንቢተኝነት የተነሣ ‹‹አቢያተ ክርስቲያናት ይትአጸዋ፣አቢያተ ጣዖታት ይትረኃዋ›› ተብሎ ታላቅ መከራ ስደትና ዕልቂት በምዕመናን ላይ ደርሷል፡፡ ለዚህ ዋነኛ ማሳያዎች ከኔሮን እስከ ዲዮቅልጢያኖስ የተነሡ ክርስቲያኖችን ያስጨፈጨፉ አሥር የሮማ ቄሣሮች ናቸው፡፡ በሃገራችንም እነ ዮዲት ጉዲት፣ ግራኝና ሱስንዮስ ይጠቀሳሉ፡፡

በነዚህ ዘመናት ቤተክርስቲያን ብዙ ቅርሶቿን ያጣችበት፣ እጠፋ እጠፋ ያለችበት ጊዜ ቢሆንም ሊቁ ጠርጡለስ ‹‹የሰማዕታት ደም የክርስቲያኖች ዘር ነው፡፡›› እንዳለውጠፋች ሲባል ሰፍታየሲዖል ደጆች ሳይችሏት ዛሬም በዓለት ክርስቶስ ላይ(1ቆሮ.10፥4) ጸንታ ቆማለች፡፡

 ሌላው አሉታዊ ተጽዕኖ ቄሣራውያን ከመናፍቃን ጋር በመተባበር በቤተክርስቲያን ላይ የሚያደርሱት ነው፡፡

ንጉሥ ቁንስጣንዲዮስ ከአርዮሳውያን ጋር በማበሩ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ከመንበሩ በተደጋጋሚ ተሰዷል፡፡ የኬልቄዶንን ጉባኤ እንዲቀበል ዲዮስቆሮስን በኃይለቃል ማስገደድ ያልቻለችው ንግሥት ብርክልያ ጽሕሙ እስኪነጭ ጥርሱ እስኪረግፍ ድረስ አስደብድባዋለች፡፡ ስለ ሰንበት አከባበር እንግዳ ትምህርት ይዘው የመጡት ቤተ ኤዎስጣቴዎስን የገደፈው ንጉሥ አምደጽዮን አባ አኖሬዎስን አስገርፎታል፡፡ ይህ ተጽዕኖ ቅዱሳን አበውን ከማንገላታት ቤተክርስቲያንን ለሁለት እስከመክፈል ድረስ ዋጋ ያስከፈለ ነው፡፡

ከሃያኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኋላበኢትዮጵያበስፋት የሚስተዋለው ተጽዕኖ ደግሞ ቄሣራዊ ኃይሎች በፍላጎታችን ይኼድልናል ብለው ያሰቡትን መለካዊ(ፍጻሜ ፈቃደ ንጉሥ) አባት ማሾም ነው። ከአቡነ ቴዎፍሎስ የግፍ አገዳደል ጀምሮ ይኼ የቄሣር ስውር እጅ በፕትርክናው መንበር ተቀማጭ አባት መረጣ ላይ ጫና እንደሚፈጥር የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ሌሎችም ብዙ አሉታዊ ጎኖች መጥቀስ ይቻላል፡፡

 በአንጻሩ ደግሞ ትሩፋትና በረከት ይዞ የመጣበትም ጥቂት ጊዜ ነበር፡፡የክርስቲያኖች ምልክት የሆነው መስቀልተቆፍሮ የወጣው ፣ ከተማረከበት ፋርስም የመጣው በቄሣራውያን ነው ፡፡(ዕሌኒና ርቃል)ጸሎተ ሃይማኖትና የሠለስቱ ምዕትን ትሩፋት ያገኘነው አርዮስም የተወገዘው ቆስጠንጢኖስ ቄሣር በተጠራ የኒቂያ ጉባኤ ነው፡፡(ንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን የተደረገውን ጉባኤና በዐፄ ዮሐንስ የተጠራው የቦሩ ሜዳ ጉባኤያቆራኟል።)ንጉሥ ዘርዐ ያዕቆብ ጉባኤ ከመጥራት ባሻገር እንደ ተአምረ ማርያም፣መጽሐፈ ብርሃንን የመሰሉ መጻሕፍትን ያበረከቱ ሊቃውንትም ሆነው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የራሷን ጳጳሳትና ፓትርያርክ እንድታገኝ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል፡፡ብዙዎች ነገሥታት እልፍ አብያተ ክርስቲያናትን አሳንጸዋል ፈልፍለውም አንጸዋል፣ገዳማትን ረድተዋል፣ርስት ሰጥተዋል፣መጻሕፍትን አስጽፈዋል። አልፎም ተርፎ ንጉሥና ቅዱስ ሆነው ፣ጽላት ተቀርፆላቸው፣ በምልጃቸው በጸሎታቸው የሚያስታርቁን እንደነአብርሃ ወአጽብሐ፣ ላሊበላ፣ ነአኵቶ ለአብ፣ ይምርሐነ ክርስቶስ፣ገብረማርያምና አድያም ሰገድ ኢያሱ የመሳሰሉ ነገሥታትም ተገኝተዋል፡፡

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በመልካም አበርክቷቸው የጠቀሟትን ያህል ከእምነት ፈቀቅ ያሉትን በሚቀጡት ተገቢ ያልሆነ ቅጣት ቤተክርስቲያንን ባልዋለችበት ባለዕዳ፣በነሱ አንጻር በዘመነኞች የሚፈረደው ፍርድ ተሸካሚ የኦሪት ፍየል አድርገዋታል፡፡(የደቂቀ እስጢፋኖስና የቦሩ ሜዳውን ቅጣት ልብ ይሏል)

በጥቅሉ በዓለምም ሆነ በኢትዮጵያም ታሪክ ቄሣራዊ ኃይሎች በቤተክርስቲያን ላይ በአዎንታም ሆነ በአሉታ ያደረሱት ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

ቤተክርስቲያን ቄሣርን በምን መልኩ ልታንጸው ወይም ተጽዕኖ ልታደርስበት ትችላለች?

ጸሎት

ቅዱስ ሐዋርያዊ አትናቴዎስ እንደተናገረው የክርስቲያኖች ትልቁ መሣርያ እጃቸውን ወደላይ ለጸሎት መዘርጋት ነው፡፡ በመሆኑም ቤተክርስቲያን የቄሣራዊ ኃይላትን መንገድ ያቀና ዘንድ ወደ እግዚአብሔር በማመልከት የሚታይ የሚጨበጥ ተጽዕኖ ልታመጣ ትችላለች፡፡

ይኼንንም የምታደርገው እንዲሁ ከጠራ ሜዳ ተነሥታ ሳይሆን እንደ ሐዋርያዊትነቷ ‹‹ልመናና ጸሎት፣ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ››(1ኛ ጢሞ 2፡1-2) የሚለውን የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስን ትእዛዝ መሠረት በማድረግ ነው፡፡

የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በሥርዓተ ቅዳሴዋ እስከ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ያሉትንን ነገሥታት በስመ ተጸውዖ እየጠራች ስታሳስብ ኖራለች፡፡ የዛሬዎቹንም መሪዎቿን በፍቅር በአንድነት ይጠብቅ በመልካም መንገድም ይመራቸው ዘንድ ትጸልያለች፡፡

ነቢዩ ኤርምያስለአረማዊውና ለጨካኙንጉሥ ናቡከደነፆር እንደጸለየ፣ሳሙኤልም እግዚአብሔርን በክፉ ምግባሩ ላሳዘነው ንጉሥ ሳኦል እንዳለቀሰለት እንዲሁ እምነተ ቢስና ምግባረ ጎዶሎ ቢሆኑ እንኳን ሃገርን ያህል ከባድ ነገር የመምራት ዕጣ በታሪክ አጋጣሚ ስለወጣላቸው እርምጃቸውም በልጆቿ ላይ የሚያሳድረው በረከትም ሆነ መርገም መኖሩ አይቀርምና በዙፋን ለተቀመጡት ሁሉ ትጸልያለች፡፡ ይኼም መሣርያዋ የጠመመውን ሲያቀና፣ የነደደውን ሲያበርድ በታሪክ ታይቷል፡፡

ሽምግልና

መቼም ትልቁ የፖለቲካው ዓለም ፍዳ በቄሣራዊ ዝሆኖች ጠብ የሚመጣ የሣሮች መጎዳት ነው፡፡ ከዓለም ፍጥረት ታሪክ ጀምሮ ለሥልጣንና ጥቅም ፉክክር ብዙዎች በመሰላቸው ወገን ተቧድነው ሲተላለቁ፣ሳንጃ ለሳንጃ ሲሞሻለቁ ብዙ ንጹሐን በመሃል ቤት እንደ ቅጠል ረግፈዋል፡፡ ይኼ መጥፎ ንባብ ከመጽሐፈ ቄሣር ብዙውን ገጽ ይወስዳል፡፡

ታዲያ ይኼ ደም መፋሰስ ከመከሰቱ በፊት “አንተም ተው፣አንተም ተው” ብሎ እርቀ ሰላም በማውረድ ብሎም ሁሉንም አካታችና አግባቢ የሆነ መፍትሔ ማፍለቁ ላይ የቤተክርስቲያን ተጽዕኖ ቀላል አይደለም፡፡

ጋይኖንስና ትሪቢጂልድ የተባሉት የጦር መኳንንት በንጉሥ አርቃድዮስ ላይ ወታደሩን በሳመፁ ጊዜ እንደኛ ሃገር የታኅሣሥ ግርግር ከፍተኛ ደም መፋሰስ እና ከባድ መሥዋዕትነት ከመከፈሉ በፊት ጋይኖንስ የቤተ መንግሥቱ የጦር ግቢ ዋና ኢታማዦር ሹም እንዲሆንናሁለቱ መኳንንት የሚፈልጓቸውን የጦር አለቆች አሳልፎ እንዲሰጥ ንጉሡን በማሳመን ሊመጣ ካለው እልቂት ሃገሪቱንና ሕዝቡን የታደጋት አሸማጋይ አባት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው፡፡

በሃገራችን ታሪክ ደግሞ አቡነ ተክለሃይማኖት በይትባረክና በይኵኖ አምላክ መሃል የነበረውን መፋጠጥ ወደ ሰላማዊ የሥልጣንና የሥርወ ምንግሥት ሽግግር በመቀየር የደሙን ጎርፍ በአባታዊ ሽምግልናቸው ገድበውታል፡፡ነገሩ ያለገባቸው አንዳንድ ምሁራን ድርጊቱን ሲወነጅሉት ሁኔታውን በሚገባ ያጠናውናያጤነው ‹‹የኢትዮጵያው ሱራፊ›› ጸሐፊ ግን ‹‹ጻድቁ በዚህ ዘመን ቢገኙ ኖሮ የኖቤል የሰላም ሽልማት ለዚህ ሥራቸው ያገኙ ነበር›› የሚል እውነተኛ ምስክርነት አስፍሯል፡፡

በተለይም በዘመነ መሣፍንት በየአውራጃው ያሉ የጎበዝ አለቆች “ክተት ሠራዊት፥ ምታ ነጋሪት” ብለው ለጦርነት ሲሰለፉ መስቀል ጨብጠው ታቦት ተሸክመው በመካከል በመግባት፥ ስመ እግዚአብሔር፣ ስመ ቅዱሳን ጠርተው ተኩስ አቁም እንዲደረግ ያደረጉ አበው እንዳሉ በእውንም በልቦለድም ዓለም ሳይቀር(ፍቅር እስከ መቃብር) አንብበናል፡፡

ዛሬም በዘመናችን በማዕከላዊ መንግሥትና የሰሜኑ ክፍል ያለውን መካረር ለመሸምገል የሃይማኖት ተቋማት ልዑክ ወደ መቐለ ማቅናታቸው የአበውን ታሪክ የሚያስታውስና ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

ቀጥተኛ ማሳሰቢያ

የመንግሥት መዋቅርና አሠራር በቀጥታ የምዕመናንና የዜጎችን የእምነት ነጻነት፣ደኅንነት የሚነካ ሲሆን ወይም ጌቶች ለሕዝቡ መጥፎ አርአያና ምሳሌ ሆነው ስተው ሲያስቱ ቤተክርስቲያን እንደሚገባ ምክር፣ተግሣፅና እርምጃ መውሰድ ይኖርባታል። ይኼም ከፍተኛ ተጽዕኖ በቄሣር ላይ ያሳድራል፡፡ ማሳሰቡምበአንድ የቤተክርስቲያን አባት ወይም በተቋም ደረጃ ሊፈጸም ይችላል፡፡ ዮሐንስ መጥምቅ ንጉሥ ሄሮድስን ‹‹የወንድምህ የፈልጶስን ሚስት ልታገባ አይገባህም›› ብሎ እንደገሠፀው፣ኃያላኑ አባ አኖሬዎስና አባ ፊልጶስ ‹‹ንጉሥ አምደ ጽዮን ሆይ የአባትህን ሚስት ልታገባ አልተፈቀደልህም›› ብለው እንደሞገቱት ግርፋትና ዕርቃን መሄድ አልፎም አንገትን መስጠት ቢያስከትልም እንኳ የነገሥታት ግላጭ የወጣ ግላዊ ነውር በስም ተጠርቶ መነወር አለበት፡፡ ደሃ ምትበድለዋን ንግሥት ‹‹አውዶክስያ ሆይ የደሃዋን መበለት ርስት መልሺ ካልሆነ ከምዕመናን አንድነት ተቀነሺ›› ብሎ ቆፍጠን ብሎ ሚናገር እንደ አፈወርቅ ያለ አባት የግድ ይላል፡፡አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ፣መጻሕፍት ሲቆነጻጸሉ፣ ምዕመናን ደማቸው እንደ ውኃ ሲፈስ ለምን አደረግህ? ለምን አስደረግህ?  ለምንስ ቸል አልህ ብሎ የሚከስ የሚወቅስ አካል ያስፈልጋታል ቤተክርስቲያን፡፡

ከክርስትና መሠረታዊ ዓላማ ጋር በማይጻረር መልኩ በተለያዩ መንገዶች ተቃውሞና ቁጣዋን በማሳየት የሃገሪቱ ግማሽ ተገዢ ሕዝብ(ከ50 ሚሊዮን በላይ) የታቀፈች ተቋም ገዢውን ኃይል በውድም ሆነ በግድ ወደ ትክክለኛው መስመር እንዲመጣ የማድረግ አቅሙ አላት፡፡

በጠላት ወረራ ሕዝባዊ አንድነትን በመጠበቅ

ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ የአድዋ ውሎ ነውና “ተዋሕድዋ” ከተሰኘው የቀደመ ዳረጎታዊ ጽሑፍ አንድ አንቀጽ እንጨልፍ።

“የውጊያና ጦርነት ቦታ የቤተ ክርስቲያን አውድማ አይደለም። ዋና ሥራዋም “ዕቀብ ሕዝባ ወሠራዊታ” ብላ ለወታደሩ መጸለይ እንጂ ወታደር መሆን አይደለም።እንደ ሕዝብና ቤተ ክርስቲያን ለሚቃጣብን የውጭ ወረራ ግን ከነገሥታት ድካም በላይ ነውና ታጥቃ ትዘምታለች። በዚህ የአንድነት ጉዳይ ካለመደራደሯ የተነሣ ያለ ቄሣር ብቻዋን የተፋለመችበት ጊዜ ሁሉ አለ።

በሁለተኛው የጣልያን ወረራ ጊዜ የፍቼው ተወላጅ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ከሰላሌ አርበኞች ጋር የተዋጉት ፣ በመጨረሻም ተይዘው ፣ ሕዝቡንና ምድሪቱን ገዝተው ለሃገር መነሣት በ፲፩ ጥይት የወደቁት ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ሸሽተው ከሃገር በወጡበት ሰዓት ነው። የጎሬው አቡነ ሚካኤል ሰማዕትነትም እንደዚያው።የተዋሕዶን የጦርነት ተሳትፎ ደግሞ መድፍ ባርካ ካዘመተችው የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እኩይ ድርጊት ነጥለን ማየት አለብን። “ለሃይማኖታችሁ ሙቱ” በሚለው የአቡነ ማቴዎስ ቡራኬና “ለሃይማኖታችሁ ግደሉ” በሚለው የሮማው ፓፓ ቃል መካከል የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት አለ። የራስን ሃይማኖት ለመጫን ብሎም እንደ ሰው የማይቆጥሩትን ሕዝብ ረግጦ ለመግዛት መዝመት ኃጢአት ሲሆን ማንነትና ሃይማኖትን ለማዳን የሚደረግ ተጋድሎ ግን የተገባ ነው።”

ስለሆነም እንዲህ ባሉ ወቅቶች  ተዋጊ አዋጊና ጸሎተኛ ሆና የመንግሥትን የመከላከል አቅም በብዙ መጠን አሳድጋለች፡፡

ሴኩላሪዝምና ቤተክርስቲያን

ቄሣርና ቤተክርስቲያን እንዳይነካኩ ማድረግ የማይቻል እንደሆነ ከታሪካዊ እውነት መገንዘብ ይቻላል፡፡ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡ መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም።” ተብሎ የሴኩላሪዝም ሕግ ቢደነገግም የሚታየው ሌላ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡

በእኔ አስተሳሰብ ከፈረንሳይ ሴኩላሪዝም የአሜሪካ ሴኩላሪዝም ለሃገራችን ይበጃታል ብዬ አምናለሁ፡፡ እንደ ፈረንሳዩ ሕግ ሃይማኖት በደረሰበት መንግሥት ዝር እንዳይል ማለት የጠበበ የመተግበር እድል ስላለው እንደ አሜሪካው አሠራር በሃይማኖት ውስጣዊ ጉዳዮች ላይ ሳይገባ የሃይማኖቶችን ዕሤቶች የሚያበረታታ መንግሥት ቢኖር መልካም ነው፡፡  ወዲህም ሃይማኖታዊ መንግሥት የሃይማኖት ብዝሃነት ባለባት ሃገር አያዋጣም። ወዲያም እግዚአብሔር ብሎ ነገር የለም የሚል ማቴሪያሊስት 99% አማኝ በሆነባት ሃገር ሲገዛ ብዙ ቀውስ ፈጥሯል፡፡

ስለሆነም ማዕጠንት እየታጠነ የሚጀመርበትም፥ ርዕሰ ብሔሩ ‹‹እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ›› ብሎ ሲናገር መሠረት እስኪነቃነቅ የሚሣቅበትም ፓርላማ ሳይሆን ለሁሉም ሃይማኖቶች እኩል የሚወግን፣ከለላና ጠበቃምየሚያደርግ፣ ቅርስና ምዕመንን ከአደጋ የሚከላለል ነገር ግን በውስጥ ጉዳይ ገብቶ የማይፈተፍት መንግሥት ያስፈልገናል ብዬ አስባለው፡፡

መጠቅለያ

ይኼ ጽሑፍ መጠቅለያ የለውም፡፡ ከአቢይ ርዕሱ የሚመዘዙ የሐሳብ ዳረጎቶች ጥርቅም ነው፡፡ አንባቢው ተቀነጫጭበው የቀረቡትን ጭማሪዎች ተመልክቶ ከሌሎችም ተወያይቶ የራሱን መደምደሚያ እንዲሰጥ የሚጠበቅበት ክፍት ጽሑፍ ነው፡፡

ከርዕሱ ክብደትና ስፋት የተነሣ ግን በሌላ ዙርና ንጻሬ መመለሴ አይቀሬ ነው፡፡ እስከዚያው

ይቆየን!

share this:

Leave a Reply