መልእክተ ዳረጎት

መልእክተ ዳረጎት

ከማሕፀነ ዮርዳኖስና ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ  ዳግም ልደታችሁ የተረጋገጠላችሁ የብርሃን ልጆች  እንደምን አላችሁ? በዚህ  በአሁኑ ጊዜ ዓለማችን አዲስ ቫይረስ ተነስቶ ከፍተኛ ጭንቀት ሲወጥራትና ከዚህ በፊት በጆራችን የሰማነውን በዐይናችን እያየን መታወክ በከበበን ሰአት  ዳረጎት ‹‹ በርናባስ ብለን የምንጠራውን የመጽናናት ልጅን››  እግዚአብሔር እንዲልክልን እንጸልይ በማለት ሊያሳስብ ይወዳል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስትያንም ወገቧን ታጥቃ፣ እጆቿን ወደጌታዋ ዘርግታ፣ ሕዝቡን በገሪዛን በረከት እንዲባርክ፣የጌባልንም መርገም እንዲያርቅ፣ የደዌ ኃይልን እንዲቀጠቅጥ፣ጽኑ ኀዘን ለወረሳቸውም  ማቅን ቀዶ ሐሴትን ሊያስታጥቅ  የሚችለው ጌታ፣ ፍጹም ብርታትን እንዲሰጣቸው  ተማኅጽኖ ላይ ትገኛለች፡፡ እግዚአብሔርም በዚህ ፈተና ውስጥ የሚጠቅመንን እንድናውቅ፤ ቆም ብለን ነገሮችን በጥልቀት እንድናስብ፣ በእኛና በእግዚአብሔር መካከል የተሰራ ጣሪያ ካለ ማስወገድን የምንወስንበት ቁርጥ ኅሊና ማግኘትን   ፣እርሱም ደግሞ ክፉውን ሁሉ ወደበጎ እንዲቀይርልን የማትጎድል ቸርነቱን የምንጠይቅበት ጊዜ ያድርግልን፡፡

ዳግመኛም እግዚአብሔር  ለህዝቡ ፈውስን እንዲያደርጉ የማዳንን ዕውቀት ያሳደረባቸውን የጤና ባለሙያዎችን  ምክራቸውን ተግባራዊ  የምናደርግበት፣ ለእነርሱም በግንባር ሆነው በሽታውን በሚጋፈጡበት ወቅት ብርታቱን እንዲሰጠቸውና የሕሙማንን ሸክም የሚሸከሙበትን ትከሻቸውን መቻልን እንዲያጎናጽፋቸው ‹ስለእነርሱ እንለምን› ሲል ያሳስባል፡፡

በመቀጠልም ዳረጎት በስድስተኛ መጽሔቷ እግዚአብሔር በረዳን መጠን የተለያዩ መልእክቶችን ያዘሉ ጽሑፎችን አካተን መጥተናል፡፡ በሁሉም ረገድ  ሁለንተናዊ መልእክት የያዙ ወቅታዊ ጉዳዮች፤ ማኅበራዊ እይታዎች፣ ታሪካዊ ኩነቶች፣ የግል ተጋድሏችንን የሚያግዙ ምእዳናት፣ ፣ለመንፈሳዊ ዕድገታችን ከኃይል ወደኃይል የምንሸጋገርባቸው መንሰላሎች ፣ ጉያችንን ዞር ብለን  እንድንፈትሽ የሚጋብዙ ግሣጼዎች፣ ዕቅበተ እምነትን የሚጮሑ አዋጆች  በአሁኑ ሥራችን ውስጥ ይገኛሉ፡፡ስለወንጌል መስፋፋት፣ ስለዓለም ሰላም ፣ ስለሀገር ደኅንነት በሆነ ጸሎታችሁ ውስጥ እኛንም እንድታካትቱንና  ጌታም በነገሮች ሁሉ መከናወንን እንዲያበዛልን በብርቱ ለምኑልን፡፡

በተረፈ ያሁኑ ሥራችን በሁለት  መንገድ ይለያል፡፡  አንደኛ ‹‹አንዳንዶቹ ጽሑፎች›› ትንሽ ዘለግ ያሉ በመሆናቸው ባታክቱ ደስ ይለናል ፡፡ያንን ያደረግንበት ምክንያት ሀሳቦቹ ግልጽ ለማድረግ ጊዜ መውሰድ ስለነበረብንና በተጨማሪም በአሁኑ ሰአት ብዙ ሰው ከመደበኛ ሥራ ያረፈ ነው ብለን ወቅታዊ ጉዳዩን ከግምት ስላስገባን ነው፡፡

ሁለተኛ የዳረጎት ድረ-ገጽ (Website) በአዲስ መልኩ አደራጅተን ተጨማሪ መልኮች አስገብተን ቴክኖሎጂውን  ለመወጃት ሞክረናል፡፡ ወደፊት ቀስ በቀስ የተለያዩ ዕቃዎችን ማስገባታችን  አይቀርም፡፡ አሁን ግን ለጊዜው የላጤን ቤት ሊያስንቅ በሚችል መልኩ  ‹‹ቤት ለእንቦሳ››  ማለት የምትችሉበት ሁኔታ ላይ አድርሰነዋል፡፡ ‹‹ Feel at home…..እንደቤትህ ቁጠረው››ይል አይደል ፈረንጅ፡፡ እናንተም ደግማችሁ ደጋግማችሁ ተመላለሱበት፡፡ ጓደኞቻችሁን አስጎብኟቻው፡፡ ሲያሻችሁ ‹‹Share ›› እያደረጋችሁ የናንተን ዳራጎት ማስፋት መብታችሁ ነው፡፡ ወደፊት ደግሞ  እንደእግዚአብሔር ፈቃድ ጡንቻ ስናወጣ በዩቲዩብ(You Tube) እንመጣና  ‹‹ነገር በዐይን ይገባል›› የተባለውን ብሒል እውነት መሆኑን እንፈትሻለን፡፡   

መልካም ንባብ፡፡

 ዲ/ን አቤል ኃይሉ(ዶ/ር)

የዳረጎት ዘተዋሕዶ  መጽሔት ዋና አዘጋጅ

share this:

Leave a Reply