መልእክተ ዳረጎት

መልእክተ ዳረጎት

ተወዳጆች ሆይ፡-

በእግዚአብሔር አብ፣ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ፣ በጌታ መንፈስ ቅዱስም ሰላም  ያላችሁ የብርሃን ልጆች እንደምን ከረማችሁ?እኛ ሁሉን በያዘው ፣ወቅትንም በሚያፈራርቀው ፣ ውሃንም በደመና ከርስ ውስጥ በሚቋጥርና ለምድር ዝናምን በሚያደርግ፣ ነፋሳትንም ከየመዛግብታቸው እያወጣ በተራሮች አናት ላይ በሚበትነው ጌታ ደኅና አለን፡፡ መግቦቱን የማይከለክልው አምላክ እናንተንም በቸርነቱ እንደሚጠብቃችሁ ተስፋችን የታመነ ነው፡፡

የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክንን አደራ ላላመብላት በተሰጠን ጸጋ መጠን የምንፍጨረጨረው ዳረጎቶች ሰባተኛ እትማችንን አጠናቀን እነሆ ስንል በታላቅ ደስታ መሆኑን ልንነግራችሁ እንወዳለን፡፡ በተፈጠረው የኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት ሥራችንን ባሰብነው ጊዜ ባናደርስም ከፆመ ፍልሰታ ጋር መገጣጠሙ ግን  ለንባብ አመቺ ጊዜ እንደሚሆንላችሁ ተሰፋ እናደርጋለን፡፡ በዚህኛው ዕትማችን ዶግማዊ ሥራዎች ፣ ወቅታዊ እይታዎች፣ የጉዞ ማስታወሻዎች፣ ተስፋን የሚያጭሩ ጽሑፎች፣ ለመንፈስ ፍሬ ቅጠል የሚሆኑ ምክሮች አካተናል፡፡ በተጨማሪም አንድ ውድ እህታችን በቋሚነት መፅሔታችን በመቀላቀል ድንቅ የሆነ ጽሑፍ አበርክታልናለች፡፡ ወደፊትም ሌሎች እህቶቸ በሰፊው የቅዱሳት አንስትን ፈለግ ተከተለው መስቀሉን ተሸክመው ወደኋላ የሌለበትን ጉዞ እንደሚቀላቀሉ ትልቅ እምነት አለን፡፡ 

በተጨማሪም በኦሮምኛ ቋንቋ ሁለተኛ የሆነውን የመጽሔት ሥራችንን በማጠናቀቅ ላይ እንገኛለን፡፡ በቅርቡ እርሱንም እንለቀዋለን፡፡

እንግዲህ ምን እንላለን? ወቅቱ ምን እንኳን አስቸጋሪና የሰቆቃው ሠልፍ ረጅምም ቢሆን ፣አንጀት የሚያርስና አንገትን ቀና የሚያደረጉ ድሎች ሁሉ ዋዜማቸው እንዲህ በመሆኑ ትንሳኤን ከመስቀል በኋላ ያደረገ አምላክ ብርቱ የሆነውን መከራ በማይመረመር ጥበቡ ቆርጦልን ሰንበታችንን እንዲያቀርብልን ከቸርነቱ ጉልበት በታች ልባችንን እናፍስሰው፡፡ ፆመ ፍልሰታውም  የተሰወረ የልባችንን መሻት የሚፈጸምበት ያድርግልን፡፡

ሰላም በዓለም ላይ!

ዲ/ን አቤል ኃይሉ(ዶ/ር)

የዳረጎት ዘተዋሕዶ  መጽሔት ዋና አዘጋጅ 

share this:

Leave a Reply